10ኛው የኢትዮጵያ ግማሽ ማራቶን ውድድር በባህርዳር ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 26፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ)10ኛው የኢትዮጵያ ግማሽ ማራቶን ውድድር ትናንት ባህርዳር ከተማ ተካሂዷል።

በሻምፒዮናው በሴቶች ታደለች በቀለ ከኦሮሚያ ማረሚያ አሸንፋለች።

ታደለች ውድድሩን በ1 ስአት ከ10 ደቂቃ 28 ሰከንድ ነው ማጠናቀቅ የቻለችው።

የኦሮሚያ ፖሊሶቹ አሸቴ በከሪ እና ጉሉሜ ቶሎሳ 2ኛ እና 3ኛ ሆነው አጠናቀዋል።

በወንዶቹ ተመሳሳይ ውድድር የኦሮሚያ ፖሊስ አትሌቱ ታምራት ቶላ በቀዳሚነት አጠናቋል።

ጌታነህ ሞላ ከመከላከያ፤ አረዶም ጥዑማይ ከመሶቦ ሲሚንቶ ታምራትን ተከትለው 2ኛ እና 3ኛ ደረጃን ይዘዋል።

በሻምፒዮናው ከ1ኛ-6ኛ ለወጡ አትሌቶች ከ20 ሺህ እስከ 3 ሺህ ብር ተሸልመዋል፡፡

በሁለቱም ፆታ አሸናፊ ለነበሩ አትሌቶች በአጠቃላይ 100 ሺህ ብር የገንዘብ ሽልማት መበርከቱን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ያደረሰን መረጃ ያመለክታል።

በውድድሩ ከኢትዮጵያ ሱማሌ ክልልና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በስተቀር ስምንት ክልሎች፣ አንድ ከተማ አስተዳደር፣ 13 ክለቦች እና በግል የተውጣጡ 79 ሴት አትሌቶችና 154 ወንድ አትሌቶች በድምሩ 233 የሚሆኑ አትሌቶች ተሳትፈዋል።