የሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ በፋሲል ከተማ ተሸንፏል

አዲስ አበባ፣ ህዳር 25፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) 4ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬም ቀጥሎ ሲካሄድ ፋሲል ከተማ፣ መከላከያ እና ሲዳማ ቡና ድል ቀንቷቸዋል።

የሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስም የመጀመሪያውን ሽንፈት አስተናግዷል።

ባለፉት ሶስት የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ማሸነፍ ያልቻለው ኢትዮጵያ ቡና ወደ አዳማ አቅንቶ ከአዳማ ከተማ 1 ለ 1 አቻ ተለያይቷል።

ወደ ጎንደር አቅንቶ በፋሲለደስ ስታዲየም ፋሲል ከተማን የገጠመው ቅዱስ ጊዮርጊስ 2 ለ 1 በሆነ ውጤት ተሸንፏል።

ሳላዲን ሰይድ ቅዱስ ጊዮርጊስን ቀዳሚ ቢያደርግም አብዱራህማን ሙባረክ እና ኤዶም ሆሶሮቪ ፋሲል ከተማን አሸናፊ ያደረጉ ግቦችን አስቆጥረዋል።

አዲስ አበባ ላይ መከላከያ በድጋሚ ሊጉን ተቀላቅሎ ጥሩ እንቅስቃሴ እያደረገ የሚገኘውን ወልዲያ ያስተናገደበት ጨዋታ ደግሞ በመከላከያ 2 ለ 0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ለመከላከያ ምንይሉ ወንድሙ እና ማራኪ ወርቁ ጎሎቹን አስቆጥረዋል።

ሲዳማ ቡና ይርጋለም ላይ ወላይታ ድቻን ገጥሞ በአዲስ ገደይ ብቸኛ ጎል 1 ለ 0 ማሸነፍ ችሏል።

በሜዳው ጅማ አባ ቡናን ያስተናገደው አርባምንጭ ከተማም 3 ለ 0 በሆነ ውጤት አሸንፏል።

ድሬዳዋ ከተማ ሊጉን በዚህ አመት የተቀላቀለውን አዲስ አበባ ከተማ አስተናግዶ 1 ለ 0 ረቷል፤ የማሸነፊያዋን ጎልም ሀብታሙ ወልዴ አስቆጥሯል።

ትናንት በተደረገ የሊጉ መርሃ ግብር በአዲስ አበባ ስታዲየም ሀዋሳ ከተማን ያስተናገደው ደደቢት በጌታነህ ከበደ ሁለት ግቦች 2 ለ 0 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።

 

 

በፋሲካው ታደሰ