የኢትዮጵያ የአውሮፕላን ማረፊያዎች የዘመነ አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያስችል የ25 ሚሊየን ብር ፕሮጀክት ተጠናቀቀ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 27፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኢትዮጵያ አራት አውሮፕላን ማረፊያዎች ዘመናዊ የሶፍት ዌር ቴክኖሎጂን በመጠቀም የተቀላጠፈ አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያስችል ፕሮጀክት ተጠናቆ ወደ ትግብራ ገባ።

የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ 24 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት ፕሮጀክት ለደንበኞች ደኅንነቱ የተጠበቀና ቀልጣፋ የኤርፖርት አገልግሎት እንዲኖር የሚያግዝ ነው።

በድርጅቱ ውስጥ ግልፅና ተጠያቂነት ያለው አሠራር እንዲኖር ከማስቻል ባለፈ ሁሉንም አገልግሎቶች በማዘመን ለተጠቃሚው ለማቅረብ ያስችላልም ተብሏል።

ፕሮጀክቱ የድርጅቱ ዋና መ/ቤትና የአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላንን ጨምሮ የድሬዳዋ፣ ባህር ዳር ግንቦት ሃያ እና መቀሌ አሉላ አባ ነጋ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያዎች በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በተደገፈ እና በመረጃ መረብ በተሳሰረ የቴክኖሎጂ ሥርዓት ሥራቸውን ለማከናወን የሚያስችል ይሆናል።

የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ቴዎድሮስ ዳዊት ቀደምት የአቪዬሽን ታሪክ ያላት ኢትዮጵያን በአውሮፕላን ማረፊያ አገልግሎት ዘርፍ ለመምራት ከሚከናወኑ ትላልቅ ፕሮጀክቶች ተጠቃሽ እንደሆነ ገልጸዋል።

ኢንዱስትሪውን ይበልጥ ለማሳደግና ዓለም አቀፍ ገበያ ውስጥ ገብቶ ለመወዳደር የተወሰደ አሠራር መሆኑን በማንሳት፥ ይህም በአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ሌላ ታሪክ ለመስራት በር የከፈተ ሂደት ነው ብለዋል።

ፕሮጀክቱን የፈፀመው የኤርነስት ኤንድ ያንግ ማኔጂንግ ፓርትነር አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያለውን ዘመናዊ አሠራር መከተሉ ድርጅቱ በአየር ትራንስፖርት ዘርፍ የበለጠ ተወዳዳሪና ብቃት ያለው እንዲሆን የሚያስችለው ነው ብለዋል።