የጅግጅጋ ዘመናዊ ቄራ ሥጋ ወደ ውጭ መላክ ሊጀምር ነው

አዲስ አበባ፣ ህዳር 26፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ በ200 ሚሊየን ብር ወጪ የተገነባው ዘመናዊ ቄራ በቅርቡ ሥጋን ወደ ውጭ መላክ ሊጀምር ነው።

ቄራው ከሁለት ሳምንት በኋላ ሥጋን ወደ ውጭ መላክ ሲጀመር የውጭ ምንዛሬ ገቢን ማሳደግ እንደሚያስችል ተገልጿል።

የቄራው ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶክተር ፋይሰል አብዲ እንደገለጹት ቄራው በአሁኑ ጊዜ ከ500 በላይ በጎችና ፍየሎችን በቀን እርድ በመፈጸም ለክልሉ ገበያ እያቀረበ ይገኛል።

በ15 ቀናት ውስጥም ወደ መካከለኛው ምሥራቅ አገራት ሥጋ በመላክ የገበያ አድማሱን ያሰፋል ብለዋል።

የጅግጅጋና የድሬዳዋ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያዎችን በመጠቀም ጥራቱን የጠበቀ ሥጋ ወደ ኳታር፣ ሳኡዲ ዓረቢያ፣ የመንና ኦማን ለመላክ ከአገራቱ ጋር ስምምነት ላይ መደረሱን ስራ አስኪያጁ ገልጸዋል።

ቄራው የማረጃ፣ የተረፈ ምርት ማስወገጃ፣ የቴክኒክና የአስተዳደር እንዲሁም የእንስሳት ማድለቢያና ማቆያ ክፍሎች የተሟላላት ነው።

ቄራው በአሁን ጊዜ ለ70 ሰዎች የስራ ዕድል መፈጠሩንና ሙሉ ለሙሉ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር 200 ሰዎች የመቅጠር አቅም ይኖረዋል ነው ያሉት ዋና ስራ አስኪያጁ።

የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱልናስር አህመድ እንደሚሉት ቄራው የክልሉ ተወላጅ በሆኑ ዳያስፖራዎች የተገነባ መሆኑን ተናግረዋል።

የቄራ ግንባታውን ያካሄዱት ዘጠኝ የክልሉ ተወላጅ ዳያስፖራዎች ሲሆኑ የክልሉ መንግሥት 6 ሚሊየን ብር ወጪ በማድረግ የመብራት ዝርጋታና የሁለት ኪሎ ሜትር ጥርጊያ መንገድ በመገንባት ድጋፍ ማድረጉን ኢዜአ ዘግቧል።