የደቡብ ክልል በሩብ ዓመቱ 1 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ሰበሰበ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 25፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የደቡብ ክልል ገቢዎች ባለስልጣን በዘንድሮው የመጀመሪያ ሩብ ዓመት 1 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ገቢ መሰብሰቡን አስታወቀ።

የባለስልጣኑ ምክትል ዳይሬክተርና የግብር ከፋዮች ትምህርትና ስልጠና ስራ ሂደት ባለቤት አቶ ወንድማገኝ ደግፌ እንደተናገሩት፥ ገቢው የተሰበሰበው በሩብ ዓመቱ ለመሰብሰብ ከታቀደው 1 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ውስጥ ነው።

የተሰበሰበው ገቢ ከእቅዱ በ16 በመቶ ቢያንስም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ24 በመቶ ብልጫ እንዳለው ተናግረዋል።

ጠንካራ የገቢ ግብር ሰራዊት በመገንባት አደረጃጀቶችን በመጠቀም የተንቀሳቀሱት የስልጤ፣ ጉራጌ ፣ ጋሞ ጎፋ፣ ሃዲያና ወላይታ ዞኖች እቅዳቸውን ከ90 በመቶ በላይና ሙሉ በሙሉ ያሳኩ ተብለው ተለይተዋል።

ካፋ፣ ሻካ፣ ጌዴኦ እና ሰገን አካባቢ ህዝቦች ዞኖች ደግሞ ዝቅተኛ አፈጻጸም ካስመዘገቡት ውስጥ የሚጠቀሱ ናቸው።

ከቅድመ ዝግጀት ምዕራፍ አንስቶ በዕቅድ ያለመመራት፣ የወጣቶችንና ሴቶችን አደረጃጀት ያለመጠቀምና ተግባራትን ማንጠባጠብ በአንዳንድ ዞኖች መስተዋሉም እንደ ክፍተት መነሳቱን ኢዜአ ዘግቧል።