የአካል ብቃት እንቅስቃሴን አዘውትሮ መስራት የሞት ተጋላጭነትን በ28 በመቶ ይቀንሳል ተባለ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 23፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ጤንነታችንን ለመጠበቅ ሲባል የአካል ብቃት እንቅስቃሴ መስራት ይመከራል፤ እውነት ግን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ረጅም እድሜን እንድንኖር ይረዳን ይሆን?

ከሰሞኑ የወጣ አዲስ ጥናት ለዚህ የሚሆን መልስ አለኝ ያለ ሲሆን፥ በሰጠው መልስም አዎ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን መስራት የሞት ተጋላጭነትን በመቀነስ ረጅም እድሜን እንድንኖር ያደርጋል ብሏል።

እንደ ጥናቱ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን አዘውትረው የሚሰሩ ሰዎች ከማይሰሩት ጋር ሲነጻጸሩ በአማካኝ የሞት ተጋላጭነታቸውን በ28 በመቶ የቀነሰ ነው ሲሉም አብራርተዋል።

በፊንላንድ የዩኬኬ የጤና ጥናት ተቋም ዶክተር ፔካ ኦጃ፥ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ለጤንነታችን መልካም መሆኑን የሚያሳዩ በርካታ መስክሮች አሉ ሲሉ ይናገራሉ።

ሆኖም ግን የዓለም ጤና ድርጅት፥ በደፈናው የአካል ብቃት እንቅስቃሴ መስራት ጠቀሜታ እንዳለው እንጂ የትኛው የበለጠ ይጠቅማል የሚለው ላይ ያለው ነገር የለም ሲሉም አስተያየታቸውን ይሰጣሉ።

“ሁላችንም ጤንነታችንን ለመጠበቅ ስንል የአካል ብቃት እንቅስቃሴ መስራትን እንመርጣለን ነገር ግን የትኛው የበለጠ ይጠቅመናል የሚለውን ለመለየት እንቸገራለን” ሲሉም ዶክተር ፔካ ኦጃ ይናገራሉ።

ዶክተር ፔካ ኦጃ እና የጥናት ቡድናቸው አዲስ በሰሩት ጥናትም የአካል ብቃት አንቅስቃሴን መስራት ለአጠቃላይ ጤንነት ያለው ጠቀሜታ ላይ ያሉ እውነታዎችን ለማስፋት መሆኑንም አስታውቀዋል።

በጥናታቸውም ከእንግሊዝ እና ከስኮትላንድ የተወጣጡ የ80 ሺህ ሰዎችን ዳታ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጣር ከ1994 እስከ 2003 በመሰብሰብ ምርምር አካሂደውበታል።

ከጥናቱ ተሳታፊዎች ውስጥም ግማሽ ያክሉ ሴቶች ሲሆኑ፥ የተሳታፊዎቹ አማካኝ የእድሜ ጣራም 52 አካባቢ መሆኑን ነው ዶክተር ኦጃ የሚናገሩት።

በጥናቱ የተሳታፊዎቹ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የመስራት ልምድ፣ የጤንነት ሁኔታቸውን እና የአኗኗር ዘይቤያቸውን ማለትም የትምህርት ሁኔታቸውን፣ የሲጋራ እና የአልኮል ተጠቃሚ መሆን አለመሆናቸውን፣ የጭንቀት መጠናቸውን ለማየት ተሞክሯል።

ከተሳታፊዎች ውስጥም 45 በመቶ ያክሉ በዓለም የጤና ድርጅት የተቀመጠውን እድሜያቸው ከ18 እስክ 65 ዓመት ሰዎች በሳምንት በአማካኝ መስራት ያለባቸውን የ150 ደቂቃ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን አሟልተው ተገኝተዋል።

የአካል ብቃት እንቅስቃሴን የሚሰራው ቡድን ምን አይነት እንቅስቃሴን አዘውትረው እንደሚሰሩ የተጠየቁ ሲሆን፥ ተሳታፊዎቹም ሳይክል መንዳት፣ የውሃ ዋና ስፖርት፣ የእግር ኳስ ጨዋታ፣ የራኬት ስፖርት ማለትም እንደ የሜዳ ቴኒስ፣ ባድሜንተን እና የመሳሰሉት እንዲሁም የኤሮቢክስ ስፖርቶችን አዘውትረው እንደሚሰሩ ምላሽ ሰጥተዋል።

ጥናቱ በአጣቃለይ ለዘጠኝ ዓመታት የተካሄደ ሲሆን፥ በዚህ ጊዜም ከተሳታፊዎቹ ውስጥ 8 ሺህ 700 ሰዎች ህይወት ማለፉን ነው ተመራማሪዎቹ የሚናገሩት።

ከነዚህም ውስጥ 1 ሺህ 900 ተሳታፊዎች ከልብ ጋር በተያያዘ ችግር ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን፥ በልብ ህመም የሞቱት ሰዎች ጥናቱ ከተጀመረ በኋላ ለልብ ህመም የተጋለጡ ናቸው ተብሏል።

ዶክተር ኦጃ እና የጥናት ቡድኑ አባላት የአካል ብቃት እንቅስቃሴን በሚሰሩት እና በማይሰሩት ሰዎች መካከል ያለውን የሞት መጠንም ያነፃፀሩ ሲሆን፥ በዚህም ማንኛውም አይነት የአካል ብቃት እንቅስቃሴን መስራት ካለመስራት የተሻለ ነው ብለዋል።

ተመራማሪዎቹ በጥናታቸው ማንኛውነም የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የሚሰሩ ሰዎች፤ ምንም አይነት የአካል ብቃት እንቅቃሴ ቢሰሩም ለሞት ተጋላጭነታቸውን በ28 በመቶ መቀነስ ይችላሉ ሲሉም ተናግረዋል።

በተለይም እንደ የውሃ ውና ስፖርት፣ ኤሮቢክስ እና የራኬት ስፖርቶች በመባል የሚታወቁት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አይነቶች ጤንነታችንን የበለጠ ለመጠበቅ ይረዳናል ሲሉም አስታውቀዋል።

ምንጭ፦ http://edition.cnn.com