ኖኪያ ነባር የሞባይል ስልኮቹን ዳግም ለገበያ አቀረበ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 23፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በቅርቡ ስማርት ስልኮችን ይፋ ያደርጋል ተብሎ የሚጠበቀው ኖኪያ ነባር የሞባይል ስልኮቹን ዳግም ለገበያ ማቅረቡ ተሰምቷል።

የፊንላንድ የሞባይል ኩባንያ የሆነው ኖኪያ የሞባይል ስልኮቹን በድረ ገጹ አማካኝነት ለገበያ ማቅረቡም ተነግሯል።

ኖኪያ አሁን ለሽያጭ ያቀረባቸው የሞባይል ስልኮች ከዚህ በፊት የነበሩ እና በርካቶች ዘንድ ተወዳጅነትን ያተረፉ ሞዴሎች መሆናቸውም ታውቋል።

ሆኖም ግን የኖኪያ አንድሮይድ ስማርት ስልኮች እና ታብሌቶች ሽያጭ በሚጀምርበት ጊዜ እንደሚቀየሩም ከኩባንያው የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

እስከዚያው ግን ኖኪያ ከዚህ ቀደም የሚታወቁ የኖኮያ ብራንድ ተወዳጅ የሞባይል ስልኮችን በድረ ገጹ አማካኝነት እንደሚሸጥ ነው ያስታወቀው።

ኖኪያ አሁን ላይ እየሰራቸው ያለውን አንድሮይድ ስማርት ስልክ እና ታብሌቶችም በወራት እድሜ ውስጥ ለገበያ እንደሚያቀርብ መግለጹ ይታወሳል።

አዳዲሶቹን የኖኪያ ስማርት ሰልኮች ዲዛይን ኤች.ኤም.ዲ / HMD Group/ በተባለ ድርጅት የተሰራ ሲሆን፥ ኩባንያው የቀድሞ ከማይክሮሶፍት እና ከኖኪያ ኩባንያ ሰራተኞች የነበሩ ሰዎች ድርጅት ነው።

ስማርት ስልኮቹ ግን ፋክስኮን የተባለ ኩባንያ አማካኝነት በቻይና እና በቬትናም እንደሚገጣጠሙም ተነግሯል።

ኖኪያ በቅርቡ ለገበያ ያቀርባቸዋል የተባሉት ስማርት ስልኮቹ አዲሱ የአንድሮይድ /Android 7.0 Nougat/ ኦፕሬቲንግ ሲስተም ይጠቀማሉ ተብሏል።

እንዲሁም 5 ነጥብ 5 እና 5 ነጥብ 2 ኢንች ኩዋድ ኤች.ዲ ኦ ሊድ ስክሪን የተገጠመላቸው ሲሆን፥ ከ22 ሜጋ ፒክስል በላይ ካሜራ ይገጠምላቸዋል።

ኖኪያ አዲስ የሚያመርታቸው ስማርት ስልኮች በቀጣዩ የካቲት ወር ለገበያ ሊቀርቡ ይችላሉ የሚሉ መረጃዎችም ወጥተዋል።

ኖኪያ ወደ ስማርት ስልከ ገበያው በሚቀላቀልበት ጊዜም በገበያው ውስጥ ተፎካካሪ ሆኖ ሊቀጥል እንደሚችልም ተገምቷል።

ምንጭ፦ ቢቢሲ